የአማራ ክፍላተሀገር ሕብረት መግለጫ
- Abebe Gelagay
- 4 days ago
- 2 min read
ከአማራ ክፍላተሀገር ሕብረት የተሰጠ የእንኳን ደስ ያላችሁና የድጋፍ መግለጫ

የአማራ ህዝብ ላለፉት ዓመታት ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ፣ ከተደገሰለት የዘር ማጥፋት እና ከከፋ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ራሱን ለመከላከል ሲል በመራራና በቁርጠኝነት የጀመረው የአማራ ህልውና ትግል፣ ዛሬ አዲስ ምዕራፍ እና ከፍታ ላይ ደርሷል። ላለፉት ሠላሣ ወራት፣ የፋኖ አደረጃጀቶች በተናጠልና በቡድን በመሆን፣ የአማራን ህዝብ ክብርና ህልውና ለማስጠበቅ እጅግ ውድ የሆነውን ህይወታቸውን ገብረው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ተጋድሎ ፈጽመዋል። ይሁንና፣ በዚህ መራራ የትግል ጉዞ ውስጥ፣ የዓላማ አንድነት ቢኖርም፣ የአደረጃጀት እና የመዋቅር ልዩነቶች የትግሉን ፍጥነት ሲገቱት፣ የአንድነትን ክንድ ሲያላሉትና ለጠላት ክፍተት ሲሰጡ መቆየታቸው አይካድም። ዛሬ ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል። የጀግንነት ጥግ፣ የአስተሳሰብ ልቀት ማሳያ የሆነው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) መመስረት፣ ትግሉን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሸጋገረ ታሪካዊ ክስተት ነው። በተለይም ሁለቱ ታላላቅ ድርጅቶች ("አፋብኃ" እና "አፋህድ") በመካከላቸው የነበረውን አጥር አፍርሰው፣ ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታትና የጋራ ራዕይን በማንገብ ወደ አንድ ውህድ ድርጅት መምጣታቸው፣ የፋኖን የፖለቲካ ብስለትና የሞራል የበላይነት በተግባር ያረጋገጠ ነው። ይህ የአንድነት ውሳኔ፡
1. የህልውና ዋስትና ነው፡- የአማራን ህዝብ ከተደቀነበት የጥፋት አደጋ በዘላቂነት ለመታደግ፣ የተበታተነ ኃይልን ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ትግሉን
በአጭር ጊዜና በአነስተኛ መስዋዕትነት ወደ ድል ለማሸጋገር ያስችላል።
2. የሀገር ቤዛ ነው፡- ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከገባችበት ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስ፣ የሰላም እጦት፤ የኢኮኖሚ ውድቀት እና የማሕበራዊ እሴት መሸርሸር
አኳያ፣ ይህ የፋኖ አንድነት ሀገሪቱን ከመከፋፈልና ከመፈራረስ የሚታደግ ብቸኛው ተስፋ ነው።
3. የብስለት ማሳያ ነው፡- የራስን ችግር በራስ የመፍታት፣ ከስሜት ይልቅ ለምክንያት የመገዛት እና ከግለሰባዊ እኔነት ይልቅ ለህዝብ ክብር የመቆም ታላቅ
የሞራል ልዕልና ነው።
ስለሆነም፣ የአማራ ክፍላተሀገር ሕብረት፣ ይህንን ጅማሮ በታላቅ አክብሮትና ደስታ እየተቀበለ፣ ለመላው የፋኖ አመራሮች፣ አባላት እና ለመላው የአማራ ህዝብ እንዲሁም ለሀገር ወዳድ የትግሉ አጋርና ደጋፊ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት ይወዳል። የአማራ ክፍላተሀገር ሕብረት፣ የፋኖን የትግል መስመር በማክበር እና ዓላማውን በመደገፍ፣ ይህ የተጀመረው የውህደትና የአንድነት ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም ትግሉ የታለመለትን የድል ጫፍ እንዲጨብጥ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግ ከጎናችሁ ይቆማል። ይህ አንድነት የጠላትን ተስፋ የሚያጨልም፣ የወዳጅን ልብ የሚያለመልም፣ ለተገፋው ህዝብ ብርሃን፣ ለወደቀች ሀገር ትንሳኤ ነው።
ድል ለአማራ ህዝብ! የአማራ ክፍላተሀገር ሕብረት
January 19, 2026











Comments